ይመስለኛል…

የሆነ ሰው ስሜት እና እውነታ የተለያዩ ናቸው ብሎ የነገረኝ ይመስለኛል፡፡ ግን ሁለቱም ተደበላልቀው መለየት ሲያቅትህ ምንድነው የሚደረገው?

እኔንጃ…ዝም ብሎ መኖር ይመስለኛል፡፡ በርግጥ እንደምታውቀው እኔ ብዙ ነገር ይመስለኛል…

አንዳንዴ በውድቅት ለሊት፤ ሰው ሁሉ በተኛበት ሰአት፤ አእምሮዬ ውስጥ ካሉት ድምጾች ውጪ ምንም በማይሰማበት ሰአት ሰላም ይሰማኛል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ በሰዎች ሳቅና ጨዋታ ተከብቤ፤ ውስጤን ስርስር የሚያደርግ ሀዘን ይሰማኛል፡፡

አንዳንዴ፤ ከአጠገቧ ሆነህ ከእንቅልፍህ ተነስተህ በፍቅር አይን የምታያት ይመስለኛል፡፡ አንዳንዴ በኔ ናፍቆት የምትሰቃይ ይመስለኛል፡፡ አንዳንዴ ስለማያስቁት ቀልዶችህ አስብና ብቻዬን እስቃለሁ፡፡ አንዳንዴ አይኗን ጨፍና በምትስቅበት መንገድ ልብህ ፍስስ የሚል ይመስለኛል፡፡ አንዳንዴ አንተ የምትጠቀመውን ቃል እጠቀማለሁ፡፡ መቼም የማይኖረንን ፍቅር እንዳስብ ያደርገኛል.. አንዳንዴ ያንን ቃል እሸሸዋለሁ… አለበለዛ ሳስታውስህ መኖሬ ነዋ!

ግን አንዳንዴ ደስተኛ የሆንክ ይመስለኛል፡፡ እሷ አታስጨንቅህም አይደል? ግራ አታጋባህም? አንዳንዴ ከኔ የተሻለች ይመስለኛል ምክንያቱም አንዳንዴ ስለጥርት ያለ ጠይም ቆዳዋ፤ ጥቅጥቅ ያለ ጥቁር አፍሮዋ እና ደግ አይኖቿ አስባለሁ፡፡

አንዳንዴ የኛ ነገር ተስፋ ያለው ይመስለኛል፡፡ አንዳንዴ ችግራችን የእሷ መኖር ይመስለኛል፡፡ ግን አንዳንዴ አንተም ለኔ እኔም ላንተ እንደማንሆን ራሴን ማስታወስ ያለብኝ ይመስለኛል፡፡

አንዳንዴ የረሳሁህ ይመስለኛል…

ግን እንዳልኩህ ብዙ ነገር ይመስለኛል፡፡