የሳሙናው አቀማመጥ አልተዋጠልኝም፡፡ ደጋግሜ ለደቂቃዎች አየሁት፡፡ የቱ ጋር ስህተት እንዳለ ማወቅ ባልችልም ቦታው ግን እዛ ጋር አይደለም፡፡ ከጎኑ የተቀመጡትን ነገሮች አየሁ፡፡ ሁለት የጥርስ ብሩሾች ከሁለት ኮልጌት ጋር ተቀምጠዋል እነሱ ትክክል ናቸው፡፡ ፎጣውስ ፎጣው ልክ እሷ እንደተወችው መሬት ላይ ተቀምጧል፡፡ ታዲያ ሳሙናው ምን ሆኗል ሌላ ሰው ነካው እንዳልል ብቻዬን ነው የምኖረው፡፡ የቤቴ ቁልፍ ያለው ሰው ደግሞ የለም፡፡ ወይ እኔ ጋር ወይ ሳሙናው ጋር በጣም ትልቅ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ አለበለዚያ ቦታው መገኘት ነበረበት፡፡
በጣም የሚያምር ቁመና ወይም መልክ አለኝ ብዬ አላስብም፡፡ አንዳንዶች ግን ቆንጆ አድርገው እንደሚያስቡኝ አውቃለሁ፡፡ አንድ ጊዜ ተነግሮኛል፡፡ ባለቤቴ የሆነ ጊዜ ቆንጆ ነህ ብላኝ ነበር፡፡ የተገናኘን ሰሞን ነበር፡፡ የዩኒቨርሲቲው ላይብረሪ ውስጥ እያጠናን ነው፡፡ ከፊት ለፊቴ ተቀምጣለች እያየችኝ እንደሆነ ባውቅም ቀና አላልኩም አጎንብሼ ማለቂያ ያላቸው ለማይመስሉት ቁጥሮች መልስ እየፈለኩ ነው፡፡ ቀስ ብላ በለስላሳ ድምጻ ቆንጆ ነህ ስትል ተሰማኝ፡፡ እንዳልሰማኋት ሆንኩ፡፡ ከቁጥር በስተቀር ሌላ ነገር እያሰብኩ ያልነበረ አስመሰልኩኝ፡፡ ቀና ብዬ እነዛን አይኖቿን ባይ እወድሻለሁ ብዬ እንደምጮህ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡
በጣም በጣም ቆንጆ ነበረች፡፡ መልኳ ከአይምሮዬ አልጠፋም፡፡ ትንሽ የህጻን የምትመስል ፊት፤ የሚያማምሩ ጥቁር አይኖች፤ ቀይ ከንፈር፤ ረዥም ጥቁር ጸጉር… እንዴት መልኳን እረሳዋለሁ ምንግዜም እንደማልረሳውም እርግጠኛ ነኝ፡፡ ማስታወስ ላይ ጎበዝ እንደሆንኩ አውቃለሁ ታዲያ ሳሙናው የት እንደነበር ለምንድነው ትዝ ያላለኝ
ሰአቴን አየሁ፡፡ ስምንት ሰአት ሆኗል፡፡ አርፍጃለው ፕሮግራሜ እየተዛባ ነው፡፡ ስምንት ተኩል ላይ ስብሰባ አለኝ፡፡ መቼም የማያልቅ ስብሰባ መጨረሻ የሌለው ስብሰባ ጥቅሙ ማይታወቅ ስብሰባ ግን መሄድ ግዴታ ነው፡፡ ከመሄዴ በፊት ግን ሻወር መውሰድ አለብኝ፡፡ የሳሙናው ነገር ግን አስጨንቆኛል ለዛም ነው ላለፉት 15 ደቂቃዎች እዚሁ ሻወር ቤት ቆሜ ያለሁት፡፡ ሶስት አመት ሙሉ በስርአት ከተቀመጠበት ዛሬ ምን ቦታውን አስቀየረው፡፡
በዚህ ሶስት አመት ውስጥ 1064 ጊዜ ሻወር ወስጃለው፡፡ 894 ገጽ ጽፌያለው፤ ከ134 ሰዎች ጋር ተዋውቄያለው፤ ዛሬን ጨምሮ ለ967 ቀናት አልቅሼያለው፡፡ የማስታወስ ችሎታዬ አለመቀነሱን አረጋገጥኩ፡፡ ሳሙናውን ግን…. እሱ ግን በቦታው አይደለም ከሶስት አመት በፊት ወደዚህ ቤት መጥቼ አስከሬኗን ሳገኝ ሳሙናው እንደዚህ አልተቀመጠም ነበር፡፡ የስልኩ ያለማቋረጥ ጢጥ ጢጥ ጢጥ የሚል ድምጽ ተሰማኝ፡፡ እሱ እንኳን አልተቀየረም፡፡ ከዛን ቀን ጀምሮ ያለማቋረጥ ለሶስት አመታት ሲጮህ ኖሯል፡፡
በቀን ውስጥ ቢያንስ አንዴ ያ ቀን ትዝ ይለኛል፡፡ ሃኒ እያልኩ ወደቤት ስገባ እሷ ደረጃው ስር መሬት ላይ በደም ተለውሳ ወድቃ ነበር፡፡ ከበሩ እንዴት እሷ አጠገብ እንደደረስኩ አላውቅም፡፡ ከአንገቷ ቀና አድርጌ ብጠራትም ልትመልስልኝ አልቻለችም፡፡ ጭራሽ አትተነፍስም፡፡ ቀሚሷ በደም ቀይ ሆኗል፡፡ ስም ለማውጣት ስንጣላበት የነበረው ልጃችን ያን ያህል ቀሎ መሬት ላይ መፍሰሱን ላምን አልቻልኩም፡፡ ምረግጥበትን ሳላውቅ ወደስልኩ በሩጫ ሄድኩ፡፡ እጀታውን እንደያዝኩ እይታዬ እየጨለመ መጣ፡፡ ወደኩ፡፡ ቤቱ እየተሽከረከረ ነበር፡፡ ስልኩ ጢጥ ጢጥ ጢጥ ሲል ሰማሁ፡፡ በወደኩበት ወደሷ ዞርኩ አትንቀሳቀስም እንባዬ ወደጎን ፊቴን እያጠበ ሲወርድ ተሰማኝ፡፡ ሁሉም ነገር ቀስ በቀስ ወደጨለማ ተለወጠ፡፡
ከዛ በኋላ ራሴን ያገኘሁት ሆሰፒታል ነበር፡፡ ከአጠገቤ ወንድሜ ተቀምጧል፡፡ ነቃህ አለኝ፡፡ አልመለስኩለትም ግራና ቀኜን አየሁ፡፡ ጠባብ መድሃኒት መድሃኒት የሚሸት ነጭ ክፍል ውስጥ ተኝቻለው፡፡ ጥያቄ ነበረኝ መልሱን ስላወኩ ግን መጠየቅ ፈራሁ፡፡ አይኖቼን ጨፍኜ በረዥሙ ከተነፈስኩ በኋላ ሃናስ አልኩት፡፡ እንባ ባቀረሩ አይኖቹ እያየኝ ጭንቅላቱን ግራና ቀኝ ወዘወዘ፡፡ ከደረጃ ላይ ወድቃ ነው፡፡ በጣም አዝናለሁ ዮኒ፡፡ የሆነ ነገር ውስጤ ሲሰበር ተሰማኝ፡፡ በህይወቴ የሱ አይነት ህመም ተሰምቶኝ አያቅም ከእንግዲህም የሚሰማኝ አይመስለኝም፡፡ በጣም ከማዘኔ የተነሳ ማልቀስ ራሱ አልቻልኩም፡፡ ማልቀስን በጣም ተመኘሁት፡፡ ካላለቀስኩ ህመሙ ሚወጣልኝ ስላልመሰለኝ….
ከቀብር ስመለስ ቤቱን እሷን እንዳስቀመጠችው ላለመቀየር ወሰንኩ፡፡ ስለሷ ምንም ነገር ትንሽም ብትሆን መርሳት አልፈለኩም፡፡ የለበሰችውን ሰማያዊ ቀሚስ፤ ጸጉሯን ያስያዘችበትን ነጭ ማስያዣ፤ ያረገችውን ጥቁር ጫማ፤ ጠዋት ስራ ከመሄዴ በፊት የሰራችልኝ ቁርስ፤ አንገቷን ወደጎን አዘንብላ አይኖቼን እያየች አፈቅርሃለሁ ያለችበትን መንገድ… ጥርት ባላለ ሁኔታ አስታውሳለሁ፡፡ ጊዜው እየራቀ ነው መሰለኝ፡፡ ሶስት አመት ብዙ ነው ማለት ነው ልረሳት ነው ማለት ነው ቀስ በቀስ ሌላም ነገር እረሳለሁ ማለት ነው ምክንያቱም ሳሙናውን እንደዚህ አላስቀመጠችም ነበር…. እርግጠኛ ነኝ ረስቻለሁ፡፡ ወደፊትም እሷን እንደምረሳት…..
😭😭😭
You are a true writer!!