“በርግጥ ገና እንዳሁኑ ሰው አፍ ውስጥ ሳልገባ ራሴ ደርሼበታለሁ፡፡ ሰው ለመቅረብ፣ ከቀረቡ በኃላ ተዝናንቶ ከአንጀት ለማውራት፣ ለመውደድ…ከዛ በላይ ደግሞ ሰውን ለማመን ረዥምምምምምምምምም ጊዜ ይወስድብኛል…. አውቃለሁ ጥሩ ነገር ነው:: ምክንያቱም የሆንኩትን ሁሉ ሆኜ ሳልማር ዛሬ ደርሶ ሰው አማኝ ብሆን አገር በኔ አይፈርድም?
የሚነገረኝን ሁሉ በሁለት ሰንጥቄ ለቀናት ሳልመርምር ብቀር አያስኮንነኝም? ሰው ባናገረኝ ቁጥር የሚያቃጭል ውሸት ውሸት የሚል ድምፅ ጭንቅላቴ ውስጥ ሳይኖር ቢቀር አይገርምም?
ፍቅር ግን የተለየ ሰው ያደርጋል፡፡
አየህ….ለመጀመሪያ ጊዜ ከተሰበርኩ በኃላ የሸሸሁትን መሰበር በገዛ እጄ ወደህይወቴ ጋበዝኩ፡፡ እንግዲህ እምነቷን፣ እድሜዋን: ስብዕናዋን ወዳ ፈቅዳ አቧራ ውስጥ ለበተነች እኔ ማን ያዝንላታል? ለእሱስ ፈልጌ የሰጠሁትን ፍቅር ካልመለስክ ብዬ እንዴት አስገድደዋለሁ? የኔን ጸባይ እንደሆን የምታውቀው ነው”
“ማንም ምንም እንዲያደርግ አታስገድጂም”
“አዎ፤ እኔም ማንም ሰው ምንም እንዳደርግ እንዲያስገድደኝ አልፈልግም”
“እሱ ግን ሁሉን ጥሎ መኖር እንዴት አስቻለው?”
“አርፋጅነቴ ረዳው:: መውደዴም መወደዴም እስኪገባኝ ጊዜ ስለሚወስድብኝ እኔ ያንን ሁሉ መንገድ ጨርሼ በወደድኩት ሰአት … የሱ ፍቅር አብቅቶ ነበር፡፡ አያሳዝንም? እድለቢስነት አይደለም? ፍቅር ግን ያበቃል እንዴ?”
“እኔንጃ…”
“ወይ ከመጀመሪያውም ፍቅር አልነበረ ይሆናል፤ ብቻ…እንደዛ ዋጋ የከፈልኩለት ነገር መጨረሻ እንደተራው…እንደተለመደው ሆነ”
“ምን?”
“ለብቻዬ ወደድኩት”
ለደቂቃዎች በዝምታ ቆዩ፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ስለሱም እንዲህ እያለች ለሌላ ወንድ ትናገር እንደሆነ እያሰበ ነበር፡፡ “ቀን ከሌት ሳይደክመው..ሊያወራኝ፣ህይወቴን… ኑሮዬን… አዋዋሌን ሊካፈል፣ ሊያገኘኝ፣ የራሱ ሊያደርገኝ ሞክሮ ተስፋ ቆረጠ” ትል ይሆን ወይስ “እንደሚወደኝ እንኳን አላውቅም ነበር ምክንያቱም ፈሪ ነው” ብላ ታማኝ ይሆን…? ምናልባት ያኔም ከረፈደ ነቅታ “አርፋጅነቴ እሱን አሳጣኝ” ብላ ስለኔ ታለቅስ ይሆናል…
ሁሉም አማራጮች ትርጉም አልሰጥ ሲሉት ወደጥያቄው ተመለሰ::
“በፍቅር ተስፋ ቆርጠሻል አይደል?”
“መሰለኝ.. ወይ ደግሞ ፍቅር ብዬ የማስበው ነገር ፍቅር አይደለም ይሆናል፤ እስከመጨረሻው የማይዘልቅ ፍቅር ፍቅር ነው? ከሆነ አልፈልገውም ይቅርብኝ”
ጭንቅላቱን በአዎንታ ነቅንቆ ዝም አለ:: እውነቷን ነው!
ፍቅር ከሆነ እሱስ መናገር ምን ያስፈራዋል? ባይሆን አይደለም?