ተምረሀል!

ከተለያየን በኋላ…ትቼህ ከሄድኩ በኋላ ምነው ምን ሆናችሁ ሲሉህ እኔን ጥፋተኛ አድርገኝ እሺ? እኔን ውቀሰኝ፡፡

መውደድም መወደድም አትችልበትም፤ ስትወደድ ትሸሻለች፤ ስትወድ አጉል ትቀርባለች፤ እንደመስታወት እንክብካቤ ትፈልጋለች፤ ልቧ ስስ ነው በላቸው፡፡

አልቃሻ ናት በትንሽ ትልቁ ታለቅሳለች፡፡ ሳቂታ ናት፤ በራሷ ቀልድ ትስቃለች፡፡ ስለሁሉም ነገር እኩል ትደሰታለች፤ እኩል ታዝናለች ብለህ ንገራቸው፡፡

የምትፈልገውን አታውቅም፤ እንደምትፈልገኝ ለማወቅ አመታት ወሰደባት፤ ያወቀች ቀን ግን እንዴት እንደምትጠላኝ ማሰብ ጀመረች፤ ስትወደኝ ልክ አልነበራትም፤ የገዛ ፍቅሯ በዝቶ እኔን አሳጣት በላቸው፡፡

ሰው እንዴት በገዛ እጁ ልቡን ይሰብራል ብለህ ጠይቃቸው!

ተወዛግባ አወዛገበችኝ፤ የጠፋ ማንነቷን ፍለጋ ራሴን አሳጣችኝ በላቸው፡፡

እርግጠኛ ነኝ አይወቅሱህም፤ ተምረሀላ! ከዚህ በኋላ አብረሀት የምትሆናት ሴት ምን አይነት መሆን እንዳለባት አሁን ተምረሀል፤ ከዚህ በኋላ አብራህ የምትሆነው ሴት የተረጋጋች ትሆናለች፤ አትጨቀጭቅህም፤ አታለቅስም፤ የት መሄድ እንደምትፈልግ ሳታውቅ ካልወሰድከኝ እያለች አታስጨንቅህም፤ ከራሷ ተጣልታ ራስህን እንድትጠላ አታደርግህም፤ ነፍሷን ሽሽት አንተን አቁስላ ቁስልህ ውስጥ አትደበቅም፡፡

ቀጣይዋ ሴት አትሰብርህም፤ ተምረሀላ!