ነብይም ባንሆን…እኔም አንተም እናውቃለን…

©Adane Firde

ነብይም ባንሆን…እኔም አንተም እናውቃለን…

መጀመሪያ አንድ እሮብ ጠዋት ላይ እንዳየኸው ትርጉም የሌለው ህልም ትረሳኛለህ። ከነመፈጠሬም አታስበኝም። ጭራሽ ወደኸኝ ታውቅ እንደነበርም ትጠራጠር ይሆናል፤ ሰው የሚወደውን ሰው እንዲህ በቀላሉ አይረሳማ!

ነብይም ባንሆን… እኔም አንተም እናውቃለን…

ቀናት ከዛም ወራት ሲያልፉ ከነአካቴው የረሳኸኝ ይመስልሀል፤ አንዲት ድሮ የምታውቃት ሴት እንደሆንኩ ይሰማሀል።

ግን ከእለታት አንድ እሁድ ነገሮች ይቀየራሉ።

‘መንገድ ላይ ብንገናኝስ?’ ብለህ በማሰብ ትጀምራለህ፡፡ ‘ምን ችግር አለው? እንደማንኛውም ሰው ሰላም ብያት አልፋለዋ!’ ቀለል ታረገዋለህ። ከዛ ግን ሳትናገር እንኳን የምታስበውን የሚያውቁት አይኖቼ ትዝ ይሉሀል። ‘አሁንም እንደድሮው ታየኝ ይሆን?’ ራስህን መጠየቅ ትጀምራለህ፤ መልሱ አዎ እንደማይሆን ግን ልብህ ያውቀዋል።

ነብይም ባንሆን…እኔም አንተም እናውቃለን…

በመስኮትህ የምትታየውን የጠዋት ጸሀይ እያየህ ስለእኔ ታስባለህ። “አሁንም ጠዋት ስትነሳ ትነጫነጭ ይሆን? እንደኔ አባብሎ የሚቀሰቅሳት ሰው አግኝታ ይሆን? ውይ እንደዛስ አይሆንም!” ከራስህ ጋር ትጣላለህ። በሌላ እቅፍ ካሰብከኝ ያምሃላ!

ነብይም ባንሆን…እኔም አንተም እናውቃለን…

የሸዋንዳኝ የቀረብኝ የሚለውን ዘፈን በሬዲዮ ስትሰማ “ካልጠፋ ዘፈን” ብለህ ትበሳጫለህ! አሁን ዘፈኑን እንደድሮው አትወደውም፤ እያንዳንዱ ስንኝ ያንተ ያልሆንኩትን እኔን ያስታውስሀላ! በሰው ፊት ስትዘፍንልኝ እንዴት አፍር እንደነበር ትዝ ይልሀል፡፡ “ሰው እንዴት አይናፋር ሆኖ ሰው አይን ውስጥ ይገባል?” ራስህን ትጠይቃለህ።

ነብይም ባንሆን…እኔም አንተም እናውቃለን…

በጠዋት ቡና ለመጠጣት ተነስተህ አሁንም ቡና የምጠጣው ከቀዘቀዘ በኋላ እንደሆነ ታስባለህ፤ ቡና እና መጽሀፍ እንዴት እወድ እንደነበር ትዝ ይልሀል። “ለመጨረሻ ጊዜ የሰጠኋትን መጽሀፍ ጨርሳው ይሆን? ማን ያውቃል? ባነበበችው ቁጥር ስለኔ ታስብ ይሆናል” ራስህን ታጽናናለህ። ማመን ባትፈልግም ልብህ ግን እንደረሳሁህ ይነግርሀል። ያማል አይደል? መረሳት ይሰብራል አይደል?

ነብይም ባንሆን…እኔም አንተም እናውቃለን…

ስልክህን አንስተህ ልትደውልልኝ ቁጥሬን ትጽፋለህ። መደወል ግን ይከብድሀል፤ ባላነሳውስ? አለመፈለግህን መቀበል እንደማትችል ስለምታውቅ ስልኩን መልሰህ ታስቀምጣለህ። “አሁንም ስልኳ ላይ ተጥዳ በሆነ ባልሆነው ትስቅ ይሆን?” ራስህን ትጠይቃለህ። “ለምን ነበር ስትስቅ ፊቷን የምትሸፍነው? ስትስቅ ደስ እንደምትለኝ መንገር ነበረብኝ” ቁጭት ቢጤ ያድርብሃል።

ነብይም ባንሆን…እኔም አንተም እናውቃለን…

ሰነባብቶ መተኛት ያቅትሃል፤ ስለኔ ማሰብ ማቆም ይከብድሃል፤ ለመጀመሪያ ጊዜ እወድሃለሁ ስላልኩበት ቀን ታስባለህ።

“እወድሀለሁ”

እንዴት በፍርሀት ጥፍሬን እየበላሁ እንዳልኩህ ትዝ ይልሀል።

“እወድሀለሁ እወድሀለሁ እወድሀለሁ”

“ምናለ ያ ጊዜ ቢመለስ!” እያልክ ትመኛለህ! ይህ ትውስታ ክብርህን ዋጥ አድርገህ እንድትደውልልኝ ያደርግሀል፡፡

ነብይም ባንሆን…እኔም አንተም እናውቃለን…

ስልኩን አላነሳም። ቁጥርህን ሳይ ልቤ እንደበፊቱ አይደነግጥም፤ እንደውም እንቅልፍ አጥቼ ስለድሮ ትዝታዎቻችን ማሰብም አቁሜያለሁ። ስምህ ከአፌ ላይ ከጠፋም ሰነባብቷል። ኧረ ለምን እንደተለያየን ካሰብኩም ቆየሁ። አሁን መንገድ ላይ ባገኘውስ ብዬ አልፈራም። የእኛ እኛን መሆን ትርጉም ይሰጥ የነበረው ድሮ እንደነበር ገብቶኛል፤ አሁን በኔ ወደፊት ውስጥ እኛ የለንም።

ነብይም ባንሆን…እኔም አንተም እናውቃለን…

ብቻህን ወደዚህና ወደዛ እየተንቆራጠጥክ “አንሺው! አንሺው! ቃል እገባለሁ ከእንግዲህ እንደሚገባሽ አድርጌ እወድሻለሁ! ከእንግዲህ አላሳዝንሽም! ከእንግዲህ ያንቺ ብቻ እሆናለሁ! አንሺው!” ትላለህ።

ነብይም ባንሆን…እኔም አንተም እናውቃለን…

ስልኩን መቼም አላነሳውም። አንተም ያጣኸውን እኔነቴን እያሰብክ ስትጸጸት ትኖራለህ።

ነብይም ባንሆን…እኔም አንተም እናውቃለን።