ሌላ ቀን

“ደህና አደርሽ?” ሞቅ ባለ ድምጽ ጠየቀኝ፡፡ ካጎነበስኩበት በፍጥነት ቀና አልኩ፡፡ የምሰራበትን ጠረጴዛ ተደግፎ ወደታች እያያኝ ነው፡፡ ከንፈሮቹን በስሱ ከፈት አድርጎ ፈገግ ብሏል፡፡ ለኔ የሰጠኝ ስሜት ግን ከፈገግታ በላይ ነበር፡፡ ሚቋረጥ በማይመስል የደስታ ጎርፍ ውስጤ ሲጥለቀለቅ ተሰማኝ፡፡ ሳላስብበት መልሼ ፈገግ አልኩለት ለጥያቄው ግን አልመለስኩለትም፡፡ አይኖቻችን በተገናኙ ቁጥር ልቤን፣ ደረቴን ሆዴን አላውቅም ብቻ ያመኛል የስቃይ ህመም ግን አልነበረም ደስስስ የሚል እያስፈራ ደስ የሚል፡፡ ቆንጆ ወንድ አይደለም፣ አቃቂር ላውጣለት ብል ብዛቱ፡፡ ወንዳወንድም አይደለም ኮራ ያለ ሰውነትም የለውም የሆነ ኮስማና ነገር ነው፡፡ ፈገግታውም የሹፈት ሚመስል፣ ፊቱ ላይ ያልታወቁ የስሜት አይነቶች ሚታዩበት፣ ያልተረጋጋ አይነት፤ ከትከሻው ጎንበስ ያለ ቁመቱም አጭር ነው፡፡ በየቀኑ ግን ጉድለቶቹ እየደበዘዙ መጡ፡፡ ሌሎች ነገሮችን ማየት ጀመርኩ፡፡ ሲስቅ አንገቱን ወደኋላ አዘንብሎ አይኖቹን ሚጨፍንበትን መንገድ፣ ሲያዋራኝ እጆቹን እርስ በርስ ሚያጠላልፍበት ሁኔታ፣ የአይኖቹ በጥቁር እና በቡኒ ቀለም መሃል መሆን፣ ድምፁ ትርጉም የማይሰጡ ነገሮችን እንዲሰጡ ማድረጉን፣ በዝምታው መሃል ሚያየኝን አስተያየት፡፡ ግን ይሄ ሁሉ የኔ አልነበረም፣ እጆቹ የኔን እጆች አልነበረም ሚይዙት፣ በዛ ድምፁ እኔን አልነበረም እወድሻለው የሚለው፣ በነዛ አይኖቹ እሷን እንደሚያያት አያየኝም፡፡ ሃሳቡ በልቤ ውስጥ የተሰካ ነገር እንዳለ ሁሉ ስብር ሲያደርገኝ ተሰማኝ፡፡

እንደሚሆን ያሰብኩበት ጊዜ ነበር፣ በአለም ላይ ደስተኛዋ ሴት እንደምሆን ያሰብኩበት ጊዜ ነበር እንደሚያስብልኝ ያሰብኩበት ጊዜ ነበር፡፡ በድንገት ብን.. ጥፍት.. ድርግም.. አለ ያ ህልም፡፡ ማርታ መጣች የኔ ህልም ተሰወረ፡፡ ማርታ ሚጎድላት ነገር አልነበረም ማወጣላት አቃቂር አልነበረኝም ምናልባትም ከምንም በላይ ያስከፋኝ እሱ ይሆናል፡፡ ትንሽ በጣም ትንሽ ስህተት ባገኝባት ለመጥላት ቀላል ይሆንልኝ ነበር ለማጥፋትም እንደዛው፡፡ እውነታው ግን ማርታ ምንም ሚቀራት ነገር አለመኖሩ ነው ያለምንም ጉድለት ትክክል ነች፡፡ ውብ፣ ቆንጆ፣ ከሰው ምትግባባ፣ ትሁት፣ ሰው አክባሪ፣ ከፊቷ ፈገግታ ማይጠፋ፣ ሰውን በቀላሉ ማሳቅ የምትችል፣ እኔ ተራ እንግዳ ተቀባይ እሷ ዶክተር ፡፡ ለምን እንደወደዳት ለማወቅ ከባድ አልነበረም፡፡ አብረው ሳያቸው መናደድ የፈለኩባቸው ቀናት ነበሩ ላጣላቸው የፈለኩበት፡፡ ከዛ ይልቅ ግን በቂ አለመሆን ነበር የሚሰማኝ፡፡ ምን ያህል ደስተኛ እንደሆኑ ሳይ ማዘን፣ መሰበር፣ ራስን መጥላት አዎ እሱ ነው ሚታየኝ፡፡ እንዴት አብረው እንደሚያምሩ እና እኔ መቼም እንደዛ ልሆን እንደማልችል በተለይም እንደሱ ካለ በሁሉ ነገሩ ከበቂ በላይ ከሆነ ሰው ጋር ታሰበኝ፡፡

እንደሁሌው ያለምንም ለየት ያለ ክስተት ቀኑ አለፈ፡፡ በሱ ሃሳብ አእምሮዬ እንደተሞላ ጠረጴዛዬ ላይ የተበታተኑትን ወረቀቶች መሰብሰብ ጀመርኩ፡፡ ለሰከንዶች ረሳሁት ስል ድንገት ለምን እንደሚመጣብኝ እያሰብኩ፡፡ ሰአቴን አየሁ “አስራአንድ ሰአት” በረዥሙ ተንፍሼ ከተቀመጥኩበት ተነሳሁ፡፡ ከአካል ድካም ግን የአእምሮ አይበልጥም? ማሰብ አያደክምም? ያውም ሻወር በመውሰድ ሆነ በመተኛት የማይጠፋ ድካም፡፡ ቦርሳዬን ይዤ ከሆስፒታሉ እንግዳ መቀበያ ዴስክ ውስጥ ወጣሁ፡፡ ፀጥ ያለው ኮሪደር ላይ ጫማዬ መሬቱን በነካ ቁጥር የሚፈጥረውን ድምፅ እየሰማሁ ተራመድኩ፡፡ እናም በድንገት እሱም አድካሚውን የስራ ቀኑን ጨርሶ ከቢሮው ሲወጣ ተገጣጠምን፡፡ እንደነርስነቱ ያለእረፍት ነው ሚሰራው በተጠራበት ክፍል ሁሉ ሲዞር ምናልባትም አንዴም ሳይቀመጥ ምግብም ሳይበላ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰውነቴ ለሱ ሲዝል ተሰማኝ፡፡ ለሰው ማዘኑን፣ አለመሰልቸቱን፣ መቼም ቅሬታ አለማቅረቡን ወደድኩለት፡፡ “አንቺም ልትወጪ ነው?” የሹፈት የመሰለ ፈገግታውን ፈገግ አለ እንደተለመደው፣ የኔም ልብ አብሮት፡፡ “አዎ እቤት ልሄድ ነው ዝም ያለ ምሽት ከአንድ ጠርሙስ ወይን ጋር ያስፈልገኛል፡፡” እቤት ስገባ ተበጥብጦ የዋለውን ቤት ማጽዳት እንሚጠብቀኝ ሳስታውስ ሳቅ አልኩ ፡፡ “ውጪው ግን እንዴት እንደሚበርድ አይተሻል? ትናንት በሙቀት ልናብድ እንደነበረ ሚያስረሳ እኮ ነው፡፡ የት እንሂድ ቆይ?” በራሱ ወሬ ሳቀ እኔም ሳኩለት አብሬው የመቆሜ ፍርሃት ሳይሆን አይቀርም ያሳቀኝ ግን፡፡ ሳቁ ሰውነቴን ውርር አደረገኝ አይኖቹ ተጨፈኑ እኔም ደስ አለኝ… ከዛም ሃዘን… ከዛም አለ’መፈለግ….. ወደውጪ ስንወጣ ንፋሱ ተቀበለን ቦርሳዬን ሚወስደው ስለመሰለኝ ወደራሴ አጥብቄ ያዝኩት፡፡ እሱን ግን ላቆመዉ አልቻልኩም። ሄደ ፤ ወደማርታ፡፡ እኔም ወደባዶ ቤቴ እንደሁሌው ብቻዬን ወደብቸኝነቴ ታክሲው ውስጥ ከተከፈተው ዘፈን ጋር እየዘፈንኩ
“ጉንፋን እኮ አይደለም የያዘኝ ፍቅር ነው…
ቀልቤ ተበታትኖ ማሰብ ተስኖኛል ሰው አርገኝ አንተ ሰው……”
ከሰአታት በኋላ ቱታዬን አድርጌ አልጋ ውስጥ ነበርኩ በብርጭቆ ወይን እና መቼ እንደምጨርሰው ማላውቀው መጽሃፍ ይዤ፡፡ እንደተለመደው ምንም አዲስ ነገር የማይፈጠርበት ምሽት፡፡ መፅሃፉ ውስጥ ባለው ገጸባህሪ ውስጥ እሱን እያየሁ ነው፡፡ የሃሳቤ ጥላ ሆነብኝ ሁሌም ሚከተለኝ የማይጠፋ ድብብቆሽ የሚጫወትብኝ፡፡ ከሰላሳ ደቂቃዎች እና ከሶስት ገጽ ንባብ በኋላ ተስፋ በመቁረጥ መጽሃፉን አስቀመጥኩት፡፡ ብርጭቆውንም፡፡ ጥቅልል ብዬ ወደ አልጋዬ ውስጥ ገባሁ ትራሱ እሱን ይሆን ይመስል፣ ብርድልብሱ ከሱ ሃሳብ ይደብቀኝ ይመስል ጥቅልል አልኩ፡፡ ከመቶ ጀምሬ ወደኋላ መቁጠር ጀመርኩ መቶ አይኖቹ ዘጠናዘጠኝ ሳቁ ዘጠናስምንት ዝምታው ዘጠናሰባት ጣቶቹ…. ከ 40 ደቂቃ እና መቶን ሶስት ጊዜ ከደገምኩ በኋላ ተኛሁ እሱን እያሰብኩ ወደሱ ወደምፈራው ህልም ወደምወደው ቅዠት….

አሁን እንደለበስኩት ነኝ… ዛሬም ማታ እንደሌሎቹ ምሽቶች ሲያየኝ አይኖቹ በሩ… አጫጭር እግሮቹ ለመፍጠን የተመቹት ባይመስልም አጠገቤ ደረሰ፡፡ እናም አቀፈኝ እቅፉ ጥንካሬ አልነበረውም ምናልባት የክንዶቹ አቅም ማጣት ይሆን? ፀጉሬ ስር ገብቶ “ደህና አደርሽ?? ሲል አንሾካሾከ አልመለስኩለትም፡፡ በመጨረሻም ለቀቀኝ እና ማርታን እንደሚያያት አየኝ አይኖቻችን ተገናኙ ራሴን ሳላይ አልቀርም ባይኖቹ ውስጥ ወይም ማርታን፡፡ ኩራት ታየኝ አይኖቹ ውስጥ መከበር መፈለግ አድናቆት እናም… ፍቅር አዎ በርግጠኝነት ፍቅር ነው…. ውስጤን ማንቀጥቀጥ ፍርሃት መልቀቅ የሚችል እይታ የዛሬውም የተለየ አልነበረም አይኖቹን በመሸሽ ፋንታ በደንብ አየኋቸው የሱን ስሜት ይሁን የኔን ፍላጎት ነጸብራቅ እያየሁ ያለሁት እርግጠኛ መሆን ፈልጌያለው ተጠጋኝ ተጠጋሁት ትንፋሹ ይሰማኝ ጀምሯል፡፡ በራስ መተማመን የሰጠኝ መሰለኝ ተጠጋሁት እጆቼ ፊቱ ላይ ነበሩ ፊቱ ይሻክራል የኔ እጆች እንጂ የሱ ፊት መሆኑን ማመን ግን አልፈለኩም፡፡ ጎንበስ ብሎ ወደከንፈሬ ተጠጋ ከንፈሮቹ ጠቁረዋል፡፡ ያጨሳል ማለት ነው? ምናልባት ቀርቤ አይቼው ስለማላውቅ ይሆናል፡፡ እናም ሳመኝ ሞቃት… ለስላሳ… የሜንት ጣእም…ህይወት…. መኖር ሚባል ነገር ካለ ይሄ መሆን አለበት… ለሆነ ያህል ጊዜ ሁሉም ነገር ልክ ሆነ….. ሰኮንዶች… ደቂቃዎች… ወይም ሰአታት ምናልባትም ቀናት አለፉ፡፡ የሆነ ስህተት እንዳለ ግን ቀልቤ ነገረኝ… ስህተት አለ…አሰብኩ፡፡ ለትንሽ ደቂቃዎች ብቻ…. ትንሽ… ከዚህ ስሜት ውስጥ መውጣት አልፈለኩም፡፡ ግን ረፍዶ ነበር…. ባነንኩ ከህልሜ ውስጥ ወጣሁ፡፡ ልክ እንደቀላል በሰከንዶች ውስጥ… ሁሉም ነገር ጥፍት…. አይኖቼን ገለጥኩ ብቻዬን ነኝ፡፡ አይ አይደለሁም… እሱም አለ ማርታም አለች እጅለእጅ ተያይዘዋል እየተሳሳቁ እኩል እየተራመዱ… እኔም እያለቀስኩ… በመከፋት ውስጥ እየተከፋሁ… በማጣት ውስጥ እያጣሁ…ሚያድነኝ ሰው በሌለበት አለም ውስጥ እየጠፋሁ… ሚያምሩትም ጥንዶች ጠፉ አሁን የእውነት ብቻዬን ሆንኩ… ብቻዬን…. ነቃሁ በደንብ ነቃሁ… ደረቴ ላይ ክብደት ተሰማኝ መተንፈስ ስራ እስኪሆንብኝ… አይኔን ድጋሚ ጨፈንኩ… ህልሜ እንዲመለስ.. መኖር እንድጀምር… ደቂቃዎች አለፉ… ክብደቱም ቀለለኝ… ትንፋሹ… የሜንቱ ጣእም… የከንፈሮቹ ሙቀት ሁሉም ጠፋ… ወደ ምንምነት ወደ ደበዘዘ ትዝታነት ተቀየረ፡፡

* * * *
ጠዋት ላይ እንደልቤ የቀዘቀዘውን ሻይ እየጠጣሁ… ከመቆየት ብዛት በረዶ የሆነውን ቁርሴን እየበላሁ ለመጨረሻ ጊዜ ህልሜን አሰብኩት… ምንም… ድብዝዝ ያለ ትዝታ ብቻ…
እናም ሳላውቀው ሌላ ቀን ሆነ… ሌላ የስራ ቀን ከጠረጴዛዬ ጀርባ በወረቀቶች ተከብቤ ቁጭ… ህልሜም ተረስቶ አእምሮዬ ቀኑን ሲያጨናንቁኝ በሚውሉት ስራዎች ተሞልቶ….. “ደህና አደርሽ?” ድምፁን ሰማሁ። ቀና ስል እነዛ አይኖች ተቀበሉኝ… ፈገግ ብዬ ተመልሼ ጎንበስ አልኩ….
ሌላ ቀን… ተመሳሳይ ቀን…እንደገና…መኖር እስክጀምር…