ከብዙ ምናልባቶች በአንደኛው…

ከብዙ ጊዜ በኋላ ገና ትናንት በህልሜ አየሁህ፡፡
ቅዠት ይሆን ህልም ያለየሁት ህልሜ እሱም ስለኔ ያልም ይሆን ብዬ እንዳስብ አደረገኝ፡፡
እናፍቅህ ይሆን? ከናፍቆቴ ብዛት እንቅልፍ አልወስድ እያለህ ተቸግረህ ይሆን? ስልክ ደውለህልኝ ከመጥራቱ በፊት ትዘጋው ይሆን? የእረፍት ቀንህ ላይ ስክር ብለህ አዲሷ ፍቅረኛህን በኔ ስም ትጠራት ይሆን? ለምን ስለሷ ታነሳለህ ብላ ትቆጣህ ይሆን? ወይስ እኔ አደርግ እንደነበረው በራስህ ጥፋት መልሳ ታባብልህ ይሆን? እስካሁን የምትወደኝ እየመሰላት ትፈራ ይሆን? እስካሁን ትወደኝ ይሆን? ኧረ ጭራሽ ወደኸኝ ታውቅ ይሆን?
እንጃ!
ስለኔ አሁንም ታስባለህ እንዴ? በየቀኑ ትዝ እልህ ይሆን? ወይስ እሁድ እሁድ ብቻ ነው?
እሁድ ምን ስትሰራ መዋል ጀመርክ? ከአልጋ ሳትወጣ ስለኔ ስታስብ ትውል ይሆን? አልጋው አሁንም እኔን እኔን ይሸታል? ለነገሩ እስካሁን ሊሸት አይችልም:: አንተ ግን የሚሸት መስሎ ይሰማህ ይሆን? አሁንም በቀኝ በኩል ነው የምትተኛው? እሷ አሁን የኔ ቦታ ላይ መተኛት ጀምራ ይሆን?
ነው ወይስ እሁድ እሁድ ጓደኞችህን ማግኘት ጀመርክ? ስለኔ ይጠይቁህ ይሆን? ሳቋ ጨዋታዋ ናፈቀን; ለምን ይቅርታ ጠይቀህ አብራችሁ አትመለሱም ይሉህ ይሆን? ወይስ ስለአዲሷ ፍቅረኛህ ቁንጅና ያዋሩህ ይሆን? እሷም እንደኔ ታስቃቸዋለች? ወይስ ባለፈው እንዳየኋት ሁሌም ኮስታራ ትሆን?
ነው ወይስ አብረን እናደርግ እንደነበረው ቤት ተቀምጠህ የታንጉት ሚስጥርን ብቻህን ታነባለህ? ለኔ ማንበብ ይናፍቅህ ይሆን? ታንጉት አሁንም እኔን ትመስልሀለች? እኔ ግን እንደታንጉት የምፈልገውን ለማግኘት ቆራጥ ነኝ እንዴ? አይደለሁም! ታዲያ ምናችን ነው የሚመሳሰለው? እሷ እኮ ገብርዬን ላለማጣት ስንቱን ሆነችው? የኔን ቶሎ ተስፋ መቁረጥ ደግሞ የምታውቀው ነው…
ሰኞስ? ጠዋት ከእንቅልፍህ ስትነሳ አጠገብህ ያለሁ እየመሰለህ ደሞ ሰኞ ደረሰ መች ነው እሁድ የሚሆነው ብለህ ልትጠይቀኝ ወደግራ ትዞራለህ? ከዛስ ስታጣኝ ይከፋህ ይሆን?
ባንለያይ ኖሮ ብለህ ትመኝ ይሆን?
ይጸጽትህ ይሆን?
ምናልባት ይጸጽትህ ይሆናል፡፡ ምናልባት እናፍቅህ ይሆናል፤ ምናልባት ከአንገቷ ጎንበስ ብላ የምትሄድ ሴት ሁሉ እኔን እየመሰለችህ ልብህ ይደነግጥ ይሆናል፤ ምናልባት አዲሷ ፍቅረኛህ ድጋሚ አብረን እንዳንሆን እድላችንን የዘጋች መስሎህ ትጠላት ይሆናል፤ ምናልባት እናፍቅህ ይሆናል፡፡
ወይ ደሞ…
ጭራሽ ትዝ አልልህ ይሆናል፡፡ ከሷ ጋር በደስታ ክንፍ ብለህ እኔን ከነመፈጠሬ ረስተኸኝ ይሆናል፤ አልናፍቅህ ይሆናል፡፡
አሁን አሁን ግን እየናፈከኝ አለመሆኑን ማሰብ እንደበፊቱ ውስጤን አያሳምመውም፡፡
ምናልባት እኔም አንተን መናፈቅ አቁሜ ይሆናል፡፡