ቃል ግባልኝ!

ታውቃለህ …ቃልኪዳን፤ ተስፋ እና ህልም የሚሉት ቃላት ድሮ ጀምሮ ያሰለቹኛል፡፡ ‹‹ጎስቋላው አለም ለመንፈሱ መጽናኛ የፈጠራቸው ወጎች›› ናቸው ብዬም ተሳልቄ አውቃለሁ፡፡
ዛሬ ግን ፍቅር ውስጥ ነኝና፤ ፍቅር ደግሞ የማታምንበትን ነገር እንድትናገር እና እንድታምን ያደርጋልና እነሆ የማታከብረውን ቃል እንድትገባልኝ እጠይቅሀለሁ፡፡
ቃል ግባልኝ…
አብረን ስንራመድ እጄን መያዝ መፈለግ ያቆምክ ቀን ልትተወኝ ቃል ግባልኝ!
እኔን መዋሸት አለመጉዳት መስሎ የተሰማህ ቀን ልትተወኝ ቃል ግባልኝ!
መደማመጥ አቁመን እኩል መጮህ የጀመርን ቀን ልትተወኝ ቃል ግባልኝ!
ወደኔ ከመምጣትህ በፊት ስልክህ ላይ ያለውን ነገር ማጥፋት የጀመርክ ቀን ልትተወኝ ቃል ግባልኝ!
አውቃለሁ ቃልህን የምታከብር ሰው አይደለህም፤ ዛሬ ግን ፍቅር ውስጥ ነኝ እና እያወኩም ቢሆን እጠይቅሀለሁ፡፡
ምንም ተስፋ ይሉት ብኩን ትልም ነፍሴ ስትሸሽ ብትኖርም..መቼም ፍቅር ውስጥ ነኝና በተስፋ ፊትህ ቆሜ እጠይቅሀለሁ፡፡
ቃል ግባልኝ!
ስደውልልህ መጀመሪያ ወደአእምሮህ የሚመጣው ቃል “ኤጭ ደወለች” መሆን ከጀመረ ልትተወኝ ቃል ግባልኝ!
ስለኔ ስታስብ የሚታይህ ደስታ መሆኑ ቀርቶ ጭንቀት የሆነ ቀን ልትተወኝ ቃል ግባልኝ!
ተጣልተን ተኮራርፈን ሳንታረቅ ማደር ከጀመርን ልትተወኝ ቃል ግባልኝ!
ሌላ ሴት ስታወራህ ልብህ መደንገጥ ከጀመረ ልትተወኝ ቃል ግባልኝ!
ስለኔ ጥርጣሬ ከተሰማህ ..ያምነኝ የነበረ ልብህ የከዳኝ ቀን ልትተወኝ ቃል ግባልኝ!
እንደ መጀመርያው የፍቅራችን ወቅት እኔን ስታይ ካልፈነደቅክ.. ደስታህ ለመሸሽ እግር ያወጣ ቀን ልትተወኝ ቃል ግባልኝ!!
በርግጥ ቃልህን የማትጠብቅ ሰው እንደሆንክ አውቃለሁ ዛሬ ግን ፍቅር ውስጥ ነኝና እያወኩም እጠይቅሀለሁ፡፡
እስካሁን ያልኩህን ሁሉ አደርጋለሁ ብለህ የማታከብረውን ቃል ግባልኝ? ምክንያቱም ፍቅር ውስጥ ስትሆን “ቃል እገባለሁ” መባል በራሱ ደስ ይላል.. የውሸትም ቢሆን፡፡
ከምንም በላይ ግን ልቤ አእምሮዬን ክዶ የማታከብረውን ቃል እንድትገባልኝ ያስገደድኩህ ቀን እኔም ላንተ፤ አንተም ለኔ አንሆንምና ልትተወኝ ቃል ግባልኝ?